ከአእምሮ ህመም ጋር ተያይዞ ብዙ ሰዎች ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አንዱ “የአእምሮ ህመም ይድናል ግን?” የሚል ነው። ለጥያቄው ምላሽ ከመስጠታችን በፊት የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች ማየት ያስፈልጋል።
1) በመጀመሪያ የአእምሮ ህመሞች ስንል ከ400 በላይ የሆኑ የተለያዩ ነገሮችን ጠቅልለን እያወራን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል።
አንዳንዶቹ ቀላል ከመሆናቸው የተነሳ ህመም ሁላ ስለማይመስሉን ህክምና ያላቸው አይመስለንም። ለምሳሌ፦ መኮላተፍ (Fluency disorders) ፣ የተወሰኑ የምግብ አይነቶችን አለመመገብ (Restrictive food intake disorder)፣ በህፃናት ላይ የሚከሰት ከእናቴ አልለይም የማለት ህመም(Separation anxiety)…ወዘተ። እንዳንዶቹ ደግሞ ከበድ ያሉ ህመሞች ናቸው። እነዚህን ሁሉ ጠቅልሎ ምላሽ ለመስጠት ስለሚያስቸግር ከ400 ህመሞች ውስጥ ተለይቶ ቢጠየቅ ለመመለስ ይቀላል።
2) አካላዊ ህመሞች ላይ “በሽታ” የሚለውን ስንጠቀም የአእምሮ ሲሆን ግን “ህመም” የሚለውን እንመርጣለን።
ምክኒያቱ ደግሞ በሽታ ሲባል መንስኤው ግልፅና ቀጥተኛ እንደሆነ ስለሚያመክት ነው። ለምሳሌ የወባ በሽታ መንስኤው የወባ ትንኝ ስትሆን ህክምናው ደግሞ ክሎሮኪይን መስጠት ነው። አንድ ሰው “የወባ በሽታ ይድናል?” ብሎ ቢጠይቅ መልሱ በቀላሉ “አዎ” የሚል ይሆናል። የአእምሮ ህመም ላይ ግን መንስኤውም ሆነ ህክምናው የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው። አስተዳደግ፣ የፍቅር ግንኙነት፣ የስራ ባህሪ፣ ሱሶች፣ የትምህርት ደረጃ፣ በቤተሰብ ውስጥ የአእምሮ ህመም መኖር…ወዘተ እንደመንስኤ ሲነሱ በህክምናው በኩል ከሚሰጠው መድሀኒት ባሻገር የስነ ልቦና የንግግር ህክምና፣ የህይወት ጫና፣ መድሀኒትን በትክክል መውሰድ፣ ሱስ…ወዘተ ተፅእኖ ያሳድራሉ።
በዚህ ምክኒያት የአእምሮ ህመሞች እንደ ክሎሮኪይን አይነት ‘ፈዋሽ’ መድሀኒት አላቸው ለማለት ያስቸግራል። በአጠቃላይ ግን አብዛኞቹ የአእምሮ ህመሞች ውጤታማ ህክምና አላቸው። ህክምናውን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርገው ደግሞ ህመሙ ሳይባባስ ባለሞያ ማማከር ነው። የአእምሮ ህክምና ግንዛቤ እንዲያድግ ስናደርግ ሰዎች ቶሎ በመሄድ ውጤታማ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንችላለን።
መልካም ጊዜ!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው