ስር ለሰደደ (chronic) ሕመም እየታከምክ ወይም ህክምናውን ልትጀምር ነው? “እስከመቼ እንዲህ ይኖራል ያን ሁላ ዓመት ክኒን ልውጥ ነው?” ብለህ ይሆን?
ሁሉም የመድሀኒት ሰው ነው!
ሰውነታችን የተገነባው ከኬሚካሎች ነው፡፡ ስራውንም የሚሰራው በኬሚካልና በኤልክትሪክ ንዝረት አመካኝነት ነው፡፡ ሰውነት የሚፈልገውን ኬሚካል ለማግኘት በየቀኑ ለሰውነታችን ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ቀላል ምሳሌ፡ ምግብና ውሀ ሳትወስድ ከሁለት ቀን በላይ የቆየህበት ቀን የለም አይደል? በየቀኑ ቢያንስ ለሶስት ጊዜ በመደበኛ ሰዓት ትመገባለህ? ማብላያ ወይ ማነቃቂ ትልና ሌላም ትጨምርበት ይሆናል፡፡ ወሀ ይጠማህና ትጠጣለህ፤ ባይጠማህም ትጠጣለህ፡፡
ምን እያደረክ መሰለህ… ሰውነትህ የሚፈልጋቸውን ኬሚካሎች በጥቅል እያቀረብክለት ነው፡፡ እንዴት አልከኝ… የምትመገበው ምግብ ይፈጭና ሀይል ይሆንሀል ወይ ሰውነትህ ያረጁ ህዋሶቹን ይተካበታል ወይ ለስራው የሚፈልገውን ኬሚካል ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ምግብ ማለት ሰውነትህ ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች ሲያልቁ እነርሱን ለመተካት የምትወስደው መድሀኒት ነው ማለት ነው።
ወደ ሰውነትህ የትኛው ይግባ ትኛው ይቅር የሚለውን የሚቆጣጠሩት ኬሚካሎች ሳይቀር ከምትበላው ምግብ የተወሰዱ አልያም ከዛ ወስዶ ሰውነትህ ራሱ ያመረታቸው ናቸው፡፡ ዛሬ ስራ የሄድከው፥ ስራህን ሰርተህ የዋልከው፣ ስትተነፍስ የዋልከው፣ ማታ እንቅልፈህ መጥቶ የተኛኸው፣ አሁን ይህንን ጽሑፍ የምታነበው… ከምግብ ተወስደው በተሰሩ ንጥረ ነገሮች አማካኝነት ነው፡፡ መድሀኒት ማለት እነዚህ ንጥረ ነገሮች መጠናቸው ሲዛባ የሚያስተካከል ወይም ሰውነታችንን በሚጎዱ ነግሮች ሲጠቃ የሚዋጋቸው ነገር ማለት ነው፡፡
ስለዚህ “ምግብ ማለት በየቀኑ የሚወሰድ የመድሀኒቶች ጥቅል ነው” የሚለው አያስማማንም? በዚህ ከተስማማን ሁሉም ሰው በየቀኑ መድሀኒት ሳይወስድ መኖር አይችልም በሚለው እንስማማለን፡፡ ምግብና ውሀ በየቀኑ መውሰድህ ነጻነትህን ወሰደው? መድሀኒት በቀን ወይም በሳምንት ወይም በወር መውሰድህስ ነጻነትህን ወሰደው?
ወተት ለዶሮ ምኗ ነው? ጥሬ ለድመት ምኗ ነው?
እኔ መስሪያ ቤት ለመድረስ የሚፈጅብኝ 40 ደቂቃ አከባቢ ነው፡፡ 5 ደቂቃ ብቻ የሚፈጅበትም አለ፡፡ ወደ 2 ሰዓት የሚፈጅበትም አለ፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ሰርተን እንገባለን፡፡ ጧት መነሳት ያለብን ሰዓት እና መሔድ የሚጠበቅብን መንገድ ርዝመት ግን የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህ 5 ደቂቃ የሚፈጅበት ሰው 2 ሰዓት የሚፈጅበት ሰው በሚነሳበት ሰዓት መነሳት ላያስፈልገው ይችላል፡፡ ዶሮም ድመትም ለመኖር መመገብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ግን ወተት ለዶሮ ምኗ ነው? ጥሬስ ለድመት ምኗ ነው? አየህ! አንዳችን ከሌላች ልዩዎች ነን፡፡ አንተም ከሌላው የምትለየው ከምግብህ ከያዘው በተጨማሪ ሚጥጥዬ ቅመም [መድሀኒት] ጣል ማድረግ ይጠበቅብሀል! ይኸው ነው።
ይመስለኛል፤ ያን ያህል ልዩ አለመሆንህን ተቀበልህ፥ መድሀኒትህን በአግባቡ መውሰድ እንዳለብህ የመቀበያው ጊዜ አሁን ነው፡፡
ከሰይጣን እና ከውሻህ ማንን ትመርጣለህ?
የውሻህን ጥቅም አልነግርህም። ካናደድከው ግን ሊነክስህም ይችላል። ውሻህ ጸባይ ከሌለው ሌላ ጸባየኛ ውሻ ታሳድጋለህ። ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ከምትገዛው የራስ ምታት ወይም የጉዞ መደሀኒት ጀምሮ ማንኛውም መድሀኒት የራሱ የጎንዮሽ ጉዳት አለው፡፡ እንደየሰው ይለያያል። በትክክል ካልተጠቀምከው ሊጎደህም ይችላል። መድሀኒቱ ካልተስማማህ ከሀኪምህ ጋር ተነጋግረህ ታስቀይረዋለህ።
ሰይጣን ያው ሰይጣን ነው። ህመም ያው ህመም ነው። ባንድም በሌላ መልኩ ይገልሀል ወይም አካል ጉዳተኛ ያደርገሀል፡፡
ስር የሰደዱ ህመሞች (ስር የሰደዱ የአእምሮ ህመሞችን ጨምሮ) ለአጭር ወይም ለረጅም ጊዜ በመድሀኒቶች ሊታከሙ ይችላሉ። ያ ማለትን ግን ዱብዳ ነው ማለትም አይደለም።
ጋሻው አወቀ (የስነ አእምሮ ባለሙያ)