ወ/ሮ እሌኒ ምስጋናው
ወ/ሮ እሌኒ ምስጋናው የአእምሮ ህክምና ተጠቃሚዎች ማህበር መስራች፣ አባልና ፕሬዝደንት ናቸው፡፡ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ድግሪ፤ በሶሲዎሎጂ የሁለተኛ ዲግሪ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ምሩቅ ናቸው፡፡ ህንድ ከሚገኘው Indian Law Society’s Law College የአእምሮ ጤና፣ ሰበዓዊ መብትና ህግ አጥንተዋል፡፡ የGlobal Mental Health Peer Network የክብር አባል እና ሜንቶር ናቸው፡፡ የወ/ሮ እሌኒ በአስራዎቹ እድሜያቸው የውጭ ሀገር የትምህርት እድል ገጥሟቸው በሚማሩበት ጊዜ በገጠማቸው ባይፖላር የሚባል ህመም ምክንያት አሁን የአእምሮ ጤና ተሟጋች ሆነው ይሰራሉ፡፡ ወ/ሮ እሌኒ ከጓደኞቻው ጋር ያቋቆሙት ማህበር ወደ 50 የሚጠጉ አባላትን ያቀፈ ሲሆን መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው ግሎባል ሜንታል ኸልዝ አክሽን ኔትዎርክ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ መቀመጫውም ካደረገው ግሎባል ሜንታል ኸልዝ ፒር ኔትዎርክ አባል ነው፡፡ ማህበሩ በዋናነት የአእምሮ ህመም ከአካላዊ ህመም የተለየ አትክሮት እንዲሰጠው ይተጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማህበሩ አባለት እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤ ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡
