አበባዋ ልጄ
ወጣቶች
ይህች ለጋ ወጣት የሀገር ልጅ ዉቢቷ
ሕመሟ እንደጥፋት ሲያስቀራት እቤቷ
በምን ተስፋ ይሆን ልቧ ሰው የሚያምነው
ከልማድስ ጫና የሚያወጣት ማነው
ሁሉም ተመልክቶ አይቶ ዝም ይላታል
ከሰው ሰራሽ ጭንቀት ማንስ ያድናታል
ከተኛበት ነቅቶ ያሰበላት ወገን
ዛሬን ለእርሷ ሰርቶ እንዲሰጣት ነገን
አባት
የአይኖቼ ማረፊያ አበባዋ ልጄ
አይን እንዳላስገባት እኔው በገዛ እጄ
መጠቋቆሚያቸው እንዳላደርጋት
ላድናት ብዬ ነው የምሸሽጋት
እጮኛ
ያለ እናት ብቻዎን ያሳደጓት ልጅዎ
ቤት ውስጥ አትደበቅ ታግዳ በደጅዎ
ብርሀን አየር አይታ ታፍና በጓዳ
እንዴት ከስማ ትርገፍ ይቺ ጽጌረዳ
አባት
ጠንቅቄ እያወኩት የዙሪያዬን ጠባይ
አውጥቼ አላሳይም ልጄን በአደባባይ
አንዴ የጣለብኝን ምን አደርገዋለሁ
ጉዴን በጓዳዬ እደብቀዋለሁ
እጮኛ
የልጅዎ በሽታ እርግማን አይደለም
ታክሞ ይድናል የአእምሮ ሕመም
የእርስዎ ርህራሄ ቢሆንም የፍቅር
ግን እቤት በድብቅ መቀመጧ ይቅር
አጎት
ስማኝ ወንድም ጋሼ ላጫውትህ ሀሳቤን
ማገዝ ስላለብኝ እኔም በተሰቤን
ታጥሮ፣ ተዘግቶባት ዘና አትልም ህይወት
እርሷም ይሻላታል ወጥታ ብትጫወት
አባት
ልጄ ሆይ አንጀቴ ስትሸበር ታማ
እጅግ ይከፋኛል ባያት ስትታማ
ቅስሟን እንዳይሰብሩት ሰዎች ስቀውባት
መጠንቀቄ እኮ ነው ክፉ እንዳይደርስባት
እጮኛ
ምንም ባላጣውም የስላቁን ጥፋት
ያለማወቅ እንጅ አይደለም የክፋት
ወገን በዚህ ጊዜ ጥሎ እንደማይጥለን
አምናለሁ ከራሱ እንደማይነጥለን
አጎት
እንለፈው እንጅ ነገሩን አብርደን
ከማን ልንኖር ነው በሰው ሁሉ ፈርደን
ጥንትም ሆነ ዛሬ ለመተሳሰቡ
ባህሉ ምቹ ነው ማህበረሰቡ
አባት
አባባሉንማ እኔስ መች አጥቼው
ዋሴ ማነው ኋላ ምስጥሬን አውጥቼው
ችግራችን ሁሉ ውርሳችን ሆኖ እንጅ
ምን መድሀኒት አለው ከሰው ለሰው ልጅ
አጎት
የእጮኛዋ ጭንቀት ይገባኛል ምንጩ
ማሰቡን አልጣም ስለውሀ አጣጩ
ዛሬን ካልደገፋት የኑሮውን አጋር
ነገ እንዴት ይመራል ህይወትን ከእርሷ ጋር
እጮኛ
መቼም በአንድ ጀንበር ሁሉ አይለወጥም
የልጅዎ ህመሟ ጫናው ጊዜ አይሰጥም
ነውና ችግሯ የማያቆያት
ይፍቀዱልኝ አሁን ሀኪም እንዲያያት
በህብረት
ከተሳሰቡበት ፈተናውም ያልቃል
በሉ እንነጋገር ሕይወት በሆነ ቃል
የቆየውን ልማድ፣ ችግር እየፈታን
በአዲስ ቋንቋ እናውራ ምራን እየመታን
ወገን ባለማወቅ መስሎ እየጨከነ
ኑሮ ማኖር ሲችል ስንቱ ሊቅ መከነ
ቆመን ስንሸኛቸው ዘመናትም ሲያልፉ
በእጃችን ነበረ የመፍትሔ ቁልፉ
ከእንግዲህ ትናንትን አስበን ከማዘን
ነገን ጥሩ እናርገው ዛሬ ላይ ተጋግዘን
መጋረጃ ገልጠን አውጥተን ሚስጢሩን
በዚች ወጣት ጥሪ፣ እንቀስቅስ ሀገሩን
እንቀስቅስ ሀገሩን
