በሌሎች ቦታ ሁነህ ራስህን አስበውና ምን እንደሚሰማህ ተመልከት፡፡ ከዚያን ለምን በዚያ መልክ ምላሽ እንደሚሰጡ ወይም ለምን እንደዛ እንደሚሆኑ ትረዳዋለህ፡፡
Navid Negahban
ድሬደዋ ዉስጥ ሲስተርስ ሚሽነሪ የሚባል የአእምሮ ማገገሚያ እና መርጃ ማዕከል አለ፡፡ ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ቅርንጫፎች ሲኖረው ይኸኛው አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ እጅግ የሚያምር ሰፊ፣ ንጹህ፣ የማገገሚያ አቅርቦት ያሉት ነው (ለምሳሌ ኳስ ጨዋታ፣ የእጅ ስራ፣ የእርሻ ስራ፣ ሙዚቃ፣ ቤተ መጽሐፍት…)፡፡ ታካሚዎች ህክምናቸውን እያገኙ በእንክብካቤ ይቆዩና ሙሉ ለሙሉ ሲሻላቸው ወደ ቤተሰብ ይሄዳሉ፡፡ ቤተሰብ ከሌላቸው ደግሞ በድርጅቱ ታቅፈው ይኖራሉ፡፡
በዚህ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ አንድ ሰው ለታካሚዎቹ የሚያደርጉት እንክብካቤ ልብ የሚሞላ ነው፡፡ እሳቸው የሚንከባከቡት መደብ በእድሜ የገፉ እንዲሁም የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ታካሚዎች ናቸው፡፡ በሚያደርጉት እንክብካቤ በርህራሔ የተሞላ ነው፡፡ አይናቸው የፍቅር እና የትግስት ጨረሮችን ይረጫል፡፡ ታካሚዎቻቸው በሰዓቱ ምግብ መመገባቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን በየጊዜው እየተከታተሉ ዉሀ ያጠጧቸዋል፤ ጸጉራቸውን ይቆርጡላቸዋል፡፡ እንቅስቃሴያቸው ሁሉ ከልብ የመነጨ ሀዘኔታ፣ መረጋጋት፣ ፍቅርና አክብሮት ያለው ነው፡፡ ጥፍራቸውን ይቆርጡላቸዋል
ርህራሄ ማለት በሌሎች ዐይን መመልከት፣ በሌሎች ጆሮ ማዳመጥ፣ በሌሎች ልብ ስሜትን ማዳመጥ ማለት ነው፡፡
Alfred Adler
አማኑኤል ሆሰፒታል ውስጥ ህክምናቸውን ተኝተው የሚከታተሉ ህሙማን ያሏቸው አስታማሚዎች፤ ለረጅም ጊዜ እዛው ሆኖ ማስታመም ስለሚቸግራቸው (በስራ ምክንያት፣ በቦታ ርቀት…) ከታማሚው ጎን እየሆነ የሚያስፈልገውን ሁሉ የሚያሟላ ሌላ አስታማሚ ሊቀጥሩ ይችላሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዲት አስታማሚ ያላት ሰብዓዊነት ልብ የሚነካ ነው፡፡ ገላቸውን አጥባ፣ በሀኪም የታዘዘቻቸውን መድሀኒቶች ገዛዝታ፣ ሰዓቱ ሲደርስ መግባ፣ ጸጉራቸውን አበጥራ ስትሰራላቸው ነው የምታዩዋት፡፡ በታካሚዎቹ ላይ የሚታየውን የህመም ስሜት ትጋራቸዋለች፣ ታባብላቸዋለች፣ ታጽናናቸዋለች፡፡ አንድ ታካሚዋ ከአእምሮው ህመም በተጨማሪ አካላዊ ህመም ስለነበረባት የህመሙ ስቃይ ሲብስባት ፊቷ ላይ በትክክል ይነበባል፡፡ ያኔ ከጀርባዋ ሂዳ ቁጭ ትልና ጸጉራን ፈትታ እያበጠረች እያሻሸችና እየሰራች አቅፋ አይዞሽ ትላታለች፡፡ ታካሚዋ ፊት ላይ የሚነበበው መጨነቅና ሲቃይ ሲቀንስ ታዩታላችሁ፡፡ ለሰው መድሀኒቱ ሰው ነው አይደል ነገሩስ፡፡ የሆስፒታሉ ሰራተኞች የሁሉንም አልጋ የሚያስተካክሉ ቢሆንም እርሷ ግን ከርሷ በስተቀር ማንም ሰው የታካሚዎቿን አልጋ እንዲነካ አትፈቅድም፡፡ ምን አልባት ራሷ ጠርጋ አንጥፋ አስተካክላ ካላስቀመጠች የመትደሰት አትመስልም፡፡
ሰብዓዊነትን ለተረዱ በእውነት ሰው ለሆኑ ለነዚህ ሰዎች ክብር ይገባቸዋል፡፡
ደግነት፣ ርህራሄ፣ ፍቅር፣ ሰብዓዊነት