በአንድ ዓረፍተነገር መተርጎም የሚከብድ ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት ጤናን እንዲህሸ ይተረጉመዋል፤ ‹‹ጤነኝነት ማለት ከበሽታ ወይም ከደካማነት ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን የተሟላ የአካል፣ የአእምሮ እና የማኅበር ደህንነት ማለት ነው››
ጤንነት ስድስት ገጽታዎች ሲኖሩት እነዚህም፡- የአካል ጤንነት፤ የአእምሮ_ጤንነት፤ የስሜት ጤንነት፣ የማህበር ጤንነት፣ የሩካቤ ጤንነት እና የመንፈስ ጤንነት ናቸው፡፡
የእእምሮ-ጤና
አእምሮ (ግእዝ ቃል) የሚለውን ቃል ለመተርጎም ከስርወ ቃሉ ብንነሳ እውቀት ማስተዋል መረዳት ማወቅ መገንዘብ የሚል ትርጉም ይሰጠናል (ኪ.ወ.ክ ግጽ 229)
አእምሮ ንቃተ ህሊናችንን፣ ትኩረታችንን፣ አስተሳሰብ አና ንግግራችንንን፣ አረዳዳችንን፣ ስሜታችንን፣ ድርጊታችንን፣ የማስታወስ አቅማችንን እና የማመዛዘን አቅማችንን የሚያጠቃልል ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ አእምሮ ከአንጎል ይለያል፡፡ ምን አልባት አንጎልን በኮምፒዩተር ሃርደዌር፣ አእምሮን በሶፍትዌሩ (በፕሮግራሙ) በመመሰል ልዩነታቸውን መረዳት እንችላለን፡፡ በእርግጥ የአእምሮችን ጤና በአንጎላችን ጤና ላይም ይወሰናል፡፡ የአእምሮ ጤናን ለመረዳት ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት መተርጎም ተገቢ ይሆናል
ንቃተ-ህሊና (Consciousness)
አከባቢያችንን የመገንዘብ ወይም የመረዳት ሁኔታ ሲሆን ስንተኛ፣ ህሊናችንን ስንስት (in comatose state) ወይም ስንሞት ይቆማል፡፡ ለምሳሌ ስንተኛ አጠገባችን ምን እየተከናወነ እንደሆነ አናውቅም፡፡
ትኩረት (Attention and Concentration)
ሀሳባችንን በሙሉ አንድ ነገር ላይ የማድረግና እና ትኩረታችንን በዛው ላይ የማስቀጠል ሁኔታ ነው፡፡
አረዳድ( Perception)
አንጎላችን ከስሜት ህዋስ (አይን፣ አፍንጫ፣ ጆሮ፣ ቆዳ፣ ምላስ…) የተቀበለውን መረጃ የማደራጀት፣ የመለየት አና የሚተረጉምገት ሁኔታ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሎሚ የመጣን ሽታ አፍንጫችን ተቀብሎ ወደ አንጎላችን ይልከውና ያ ነገር ሎሚ ይሁን ወይም ሌላ ነገር ይሁን መረዳት እንችላለን፡፡
አስተሳሰብ እና ንግግር (thought and speech)
ማሰብ ማለት በጭንቅላታችን ውስጥ ነገሮችን ማሰላሰል፣ መገምገም፣ ማመዛዘን፣ አመክንዬ መስጠት፣ በምዕናብ መሳል ማለት ሲሆን በጭንቅላታች ያሰላሰልነውን ነገር በንግግር ለሰው እንገልጸዋለን ወይም እናወጣዋለን፡፡
ስሜት (emotion)
በአከባቢያችን ወይም በውስጣችን ለሚኖሩ ለውጦች የምናሳየው ወይም በውስጣችን የምንይዘው ድርጊትን ወይም ስሜትን ወይም መንፈስን ያጠቃልላል::
ድርጊት (Action)
አንድን አላማ ያለው ነገር ለማድረግ የምናከናውነው፤ በፍላጎታች የሚመራ እንቅስቃሴ ወይም ሁነት ነው፡፡
የማስታወስ-አቅም (Memory)
መረጃን የመተርጎም፣ የማጠራቀምና በምንፈልገው ጊዜ ከአእምሯችን በማውጣት (በማስታወስ) መጠቀም ነው፡፡
ማመዛዘን (Judgement)
ሁለት እና ከዛ በላይ በሆኑ ነገሮችን ላይ መምረጥ ወይም ዉሳኔ መወሰን እና ትርጉም ወዳለው ማጠቃልያ መምጣት ማለት ነው፡፡
አእምሮአችን ጤናማ ነው ስንል ከላይ የጠቀስናቸው ነገሮች ጤናማ ናቸው ማለታችን ነው፡፡ አንድ ሰው የአእምሮ ህመም ሲገጥመው ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች ላይ ያልተለመደ ለውጥ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ የማይታይን ነገር ‹‹አየሁ››፣ የማይሰማን ነገር ‹‹ሰማሁ›› ሲል፣ ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥርጣሬ ሲያሳይ፣ ምንጭ የለለው የተጋነነ ደስተኝነት ሲኖረው፣ በጣም ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ሲያወራ ሊስተዋል ይችላል፡፡
የአእምሮ ጤና በህይወታችን የሚገጥሙን ዉጣ-ዉረዶች ስሜታችን፣ አስተሳሰባችን እና ባህሪያችን ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱብን ማለፍ መቻል ነው፡፡ አንድ ሰው የሚገጥሙትን የህይወት ጫናዎችን መቋቋም ሲችል፤ ችሎውንና አቅሙን መረዳት ሲችል፤ ፍሬያማ ሕይወት መምራት ሲችል እና ከሚኖበት ማኅበረሰብ ውስጥ መግባባት ሲችልና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤ መምራት ሲችል የአእምሮ ጤና አለው ይባላል፡፡
አዘጋጅ፡ ጋሻው አወቀ (የስነ አእምሮ ባለሙያ)