
ህክምናው
የድባቴ ህመም (depressive disorder) ውጤታማ ህክምና አለው፡፡ የህመሙ አይነት ቀለል ያለ ከሆነ ከመድሀኒት ይልቅ ሌሎች አማራጮች ይኖሩታል፡፡ ለምሳሌ፡-
- ራስን መንከባከብ፣ በቂ ምግብ መመገብ፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘት
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
- መንፈሳዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ማጠንከር
ህመሙ ደረጃው ከፍ ያለ ከሆነ ግን የተለያዩ የህክምና አማራጮች አሉት፡፡
የንግግር ሕክምና (psychotherapy)
የድባቴ (ዲፐረሽን) ህመምን ለማከም ውጤታማ የሆኑ የተለያዩ የንግግር ህክምና አይነቶች አሉ፡፡ የህመሙ መነሻ ተፈጥሯዊ (biological) ስነ ልቦናዊ (የስብዕና አይነት፣ ጭንቀትን የመቆጣጠር አቅም አናሳ መሆን…) እና ማህበራዊ (አስጨናዊ ሕወት ገጠመኞች፣ አጋዥ ሰው በማጣት…) እንደመሆኑ መጠን የነዚህን በማጥናት ለህመሙ እንዴት መነሾ እንደሆኑ በመገንዘብና በማከም ረገድ የንግግር ህክምናዎች አይነትኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ የንግግር ህክምናዎች ብቻቸውን ወይም ከመድሀኒት ጋር አብረው ይሰጣሉ፡፡ እነዚህም በሙያው በሰለጠነ የንግግር ሀኪምና ባለሞያ (psychotherapist)፣ በአእምሮ ሃኪም (psychiatrist) እንዲሁም በሌሎች የሰለጠኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይሰጣል፡፡
የመድሀኒት ክህምና (pharmacological treatment)
የጸረ-ድብርት መድሀኒቶች በብዙ አማራጮች አሉ፡፡ ከንግግር ክህምና ጋር ሲሰጡ ደግሞ የበለጠ ውጤት አላቸው፡፡ የጸረ ድብርት መደሀኒቶች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ከ1-2 ሳምንታት ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ምልክቶቹ እየጠፉልን እንደሚመጡ ልንገነዘብ ይገባል እንጅ ህክምናው እንደተጀመረ ወዲያውኑ ምልክቶቹ አይጠፉልንም፡፡ አንድ ያልታከመ የድባቴ ምዕራፍ (untreated depressive episode) ከ6-13 ወር ሊቆይ ይችላል (ከ6ወር እስከ 2ዓመት የሚሉም አሉ) ከዚያ በኋላ ለተወሰነ ጊዜያት ይጠፋና መልሶ ያገረሻል፡፡ የማገርሸት ድግግሞሹና የህመሙ አደገኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይመጣል፡፡
እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ህመሙ ምንም እንኳን ሄድ-መጣ የሚል ባህሪ ቢኖረውም ህመመተኞች በህመሙ ወቅት የህመሙን ምልክቶች ፈጽሞ ሊቋቋሟቸው ስለማይችሉ ስራቸውን፣ ኑሯቸውን፣ ትዳራቸውን፣ እርግፍ አድርገው በመተው ብቻቸውን መሰቃየት ይቀጥላሉ፡፡ በመጨረሻም ራሳቸውን በማጥፋት ልናጣቸው እንችላለን፡፡ ሳንታከም በቆየን ቁጥር ህመሙ እየተወሳሰበ፤ ለመታከም የሚያስፈልገው ጊዜም እየጨመረ ይመጣል፡፡ ህመሙ በቶሎ ታውቆ ወደ ህክምና ከመጣ ግን ህክምናው የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ህክምናውን በአግባቡ የምንከታተል ከሆነ ህክምናወን በጀመርን በሳምንታት ውስጥ የጤና መሻሻል እናሳያለን፡፡ ህክምናችንን በጀመርን በ3 ወር አከባቢ ወደ ጤናችን እንመለሳለን፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ወደቀጣዩ የክህምና ደረጃ የምንሸጋገር ሲሆን ይህም በሀኪማችን የሚወሰን ይሆናል፡፡
ሌላው ጉዳይ፤ ጸረ ድባቴ መድሀኒቶች ለማቋረጥ ወይም ለማቆም ሲፈለግ ቀስ በቀስ መጠናቸው እየተቀነሰ ነው፡፡ ጸረ-ድባቴ መድሀኒቶች ምንም እንኳ የሱስነት ባህሪ ባይኖራቸውም ወዲያው ብናቋርጣቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች (discontinuation syndrome) ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የህመሙ ምልክቶች ይመለሱብናል፡፡ ስለዚህ ሀኪም ሳያዝ ማቆምም ሆነ ማቋረጥ አይመከርም፡፡ በሀኪም ሳይታዘዝም መጠቀም መጀመር በፍጽም አይመከርም፡፡ የአእምሮ ህመም መድሀኒቶች ታማሚው ጋር ከሚቀመጡ ይልቅ ቤተሰብ ጋር ተቀምጠው በቤተሰብ ክትትል መሰጠት ነው ያለባቸው፤ ምክንያቱም አንዳንድ ህመምተኞች መድሀኒቶቹን በአግባቡ የማይወስዱ ከመሆኑ በተጨማሪ በከፍተኛ መጠን ከተወሰዱ ጉዳት የሚያመጡ መድሀኒቶች ስላሉ ነው፡፡ ሱስ የሆኑ ነገሮችን (አልኮል፣ ሲጋራ፣ ጫት…) ማቆም እንደ ቡና እና ሻይ ያሉ አነቃቂ ነገሮችን ደግሞ መቀነስ ያስፈልጋል፡፡
የንዝረት ህክምና (Electroconvulsive therapy)
የንዝረት ህክምና ደረጃቸው ከፍ ላለ ህመሞች፣ በመድሀኒት ለመታከም ላስቸገሩ ህመሞች፣ መድሃኒቶችን መውስድ የማይችል ህመምተኛ ካጋጠመን ወይም በጣም አስቸኳይ ህክምና ለሚሹ የአእምሮ ሕመሞች የሚሰጥ የህክምና አይነት ነው፡፡ በንግግር እና በመድሐኒት ህክምና ያልታከመ/ያስቸገረ ድባቴ (ድፕረሽን) በንዝረት ህክምና ይድናል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም ሌሎች የህክምና አማራጮች አሉ፡፡
የማጠቃልያ ሀሰቦች
- የድባቴ ህመም መርገም ወይም የግለሰቡ ድክመት ሳይሆን ስነ ሕወታዊ፣ ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ መነሾ ያለው መታከም የሚችል ህመም ነው፡፡
- በድባቴ ህመም ላመታመም ማንም ዋስትና የለውም፡፡
- ቤትዎ አይደበቁ፣ ብቻዎትን አይደሉም፤ ህክምናውን ማግኘት ይችላሉ፡፡
ጋሻው አወቀ (የስነ አእምሮ ባለሙያ)