ሽቅለት (Mania) ባልተለመደ ሁኔታ የተጋነነ የደስታ እና በሀይል የመሞላት ስሜት ነው፡፡ ሽቅለት ያለበት ሰው ያለምንም ምክንያት ከልክ ያለፈ ደስትኘት፣ ‹‹ሁሉን እችላለሁ፤›› ‹‹ማን እንደኔ›› ባይ ይሆናል፡፡ በእርሱ ተቃራኒ የሆኑ ሃሳቦች ተቃውሞ ከገጠማቸው ወይም የሆነ ነገር ፈልጎ ከተከለከለ፤ ከክልከላው ጋር የማይመጣጠን (የተጋነነ) መነጫነጭና እልክ መጋባት ውስጥ ይገባል፤ እቃ ወደ መሰባበር ወይም ወደ ጠብ ሊያመራም ይችላል፡፡
በእርግጥ አንድ ሰው አንዳንዴ ከልክ ያለፈ ደስታ ውስጥ ሊገባ ቢችልም፤ ከመጠን ያለፈው ደስታው ከአንድ ሳምንት በላይ ከበለጠና ሌሎች ተያያዥ ምልክቶች የሚያሳይ ከሆነ የስሜት-ወዋዠቅ 1 (bipolar one disorder) በተባለ ሕመም መያዙን ያሳያል፡፡ ህመምተኛው ደስታው ከልክ እንዳለፈና የሚናገራቸው ነገሮች መሰረተ ቢስ እንደሆኑ አይረዳውም፡፡ ለምሳሌ በጣም ታዋዊ ከሆነ አርቲስት ወይም ፖለቲከኛ ጋር አንድም ቀን ተዋውቃ የማታቅ ሴት፤ አርቲስቱን (ፓለቲከኛውን) ባለቤቴ ነው ወይም የስራ ባልደረባው ነኝ ብላ ችክ (ድርቅ) ልትል ትችላለች፡፡ ለእርሷ ይህ እምነቷ መሰረተ ቢስ እንደሆነ አትረዳውም፡፡ ይች ሴት ቀለሙ ያልተመጣጠነ ወይም እጅግ ቦግ ያለ ልብስ ለብሳ፣ እጅግ የበዛ ሜካፕ ተጠቅማ ወይም አላስፈላጊ ጌጣጌቶችን ደርድራ ልናያት እንችላለን፡፡
ከመጠን ካለፈ ደስታ፣ መነጫነጭ እንዲሁም በሀይል ከመሞላት (energetic) በተጨማሪ የሚከተሉት ምልክቶች ሲኖሩ ሽቅለት (mania) እንላለን፡፡
ራስን መኮፈስ (Grandiosity)
ሽቅለት ያለበት ሰው ራሱን ከማንኛም ሰው የበለጠ ሀብታም፣ ቆንጆ፣ ሁሉን ቻይ፣ አዋቂ፣ አስፈላጊ… አድርጎ ያስባል፡፡ የሌለውን ነገሮች አለኝ፣ የማያውቀውን ነገሮች አውቃለሁ፣ ማድረግ የማይችላቸውን ነገሮች ማድረግ እችላለሁ ሲል ይስተዋላል፡፡ የሰውን ንብረት የኔ ነው ብሎ ሊከራከር ወይም ጸብ ሊያነሳም ይችላል፡፡
መተኛት አለመፈለግ (decreased sleep need)
ህመምተኛው ከ24 ሰዓታት ውስጥ፤ ለምሳሌ፣ ለ3 ሰዓት ብቻ ሊተኛ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ እንደተኛ ሊሰማው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሌሊት ሰው በሚተኛበት ሰዓት የታጠበ ልብስ መልሶ ሲያጥብ፣ የጸዳ ቤት መልሶ እያጸዳ ወይም አላስፈላጊ የሆነ ስራ ሲሰራ ሊያድር ይችላል፡፡ የህመሙ ምልክት ሲብስ ህመምተኛው ለተከታታይ ቀናት ምንም ሳይተኛ ድካም በጭራሽ ላይሰማው ይችላል፡፡
ወሬኝነት (talkativeness)
ህመምተኛው ለመከታተል በሚችገር ፍጥነት ማውራት፣ በሀይልና በታመቀ ሁኔታ ማውራት ይጀምራል፡፡ የሚያወራውን ወሬ ለማቋረጥ አስቸጋሪ ነው- እኔ ብቻ ላውራ ስለሚል፡፡ ሀሳቡን ለማቋረጥ ከተሞከረ ወይም ትክክል አይደለህም ከተባለ ወደ ግጭት ሊገባ ይችላል፡፡ አንዳንዴ የሚያበሽቁ ቀልዶችን ወይም ሳቆችን፣ ሙዚቃዎችን ሊጫወት ይችላል፡፡
ከሀሰብ ሀሳብ መዝለል (flight of idea)
በሚናገርበት ጊዜ፤ ስለ አንዱ ሀሳብ ተናግሮ ሳይቸርስ ሌላ ሀሰብ ይጀምራል፤ እሱንም ሳይጨርስ ወደሌለው ይሄዳል፡፡
በቀላሉ መረበሽ (Distractibility)
ጥቃቅን ነገሮች ሀሳቡን ይሰረቁታል፡፡ ትዕዛዝ መከተል እንዲሁም በአግባቡ ንግግር ውስጥ መቆየት አይችልም፡፡
የበዛ ግብ ያለው እንቅስቃሴ (increased goal directed activity)
ብዙ ያቅዳል (ከአቅሙ በላይ)፣ ብዙ ስረዎች አንድ ጊዜ ይጀምራል፡፡ የጀመራቸውን ትቶ ሌላ ይጀምራል፡፡ ከፍ ያለ የሩካቤ ፍላጎት እና ልቅ የሆነ ግብረ ስጋ ግንኙነት (increased sexual drive or intercourse) ይኖረዋል፤ ይቅበጠበጣል፣ በየመንገዱ ካገኘው ሰው ጋር ይተዋወቃል፣ ይቀራረባል፣ የሚጠቅመውን የማይጠቅመውንም ይገዛል፣ ገንዘብ ለዚህም ለዛም ይሰጣል፣ ያገኘውን ይጋብዛል….
ህመም የሚያስከትሉ እንቅስቃሴዎች (pain resulting activities)
ልቅ የሆኑ እንዲሁም ጉዳት ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ እናየዋለን፡፡
ጋሻው አወቀ (የስነ አእምሮ ባለሙያ)