አንዲት ታካሚ ከተናገረችው
ቴዲ አፍሮ ከኔ ፍቀር ይዞት ሊያገባኝ ይፈልግ ነበር፡፡ ቬሎ ለብሼ እንዲወስደኝ እየጠበቁት ነበር ነገር ግን ቤተሰቦቼ ተመቅኝተው እዚህ ሆስፒታል በማስገባት ከእርሱ እንድለይ አደረጉኝ
የተሳሳተ ፅኑ እምነት (delusion) ማለት ሊናወጥ የማይቻል የተሳሳተ እምነት ማለት ነው፡፡ የተሳሳተ ፅኑ እምነት ያለው ሰው አስተሳሰቡ ከታካሚው ማኅበራዊ እና ባህላዊ ዳራ ጋር ያልተጣጣመ ነው፡፡ ለምሳሌ በክርስትና እምነት ተከታይ የሆነ አንድ አማኝ ‹‹አምላክ ተገለጠልኝ›› ቢል የመታመን እድል ሊኖረው ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሀይማኖት የጸኑ ሰዎች እንደ ቅድስናቸው አምላክ ሊገለጥላቸው እንደሚችል ሀይማኖቱ ያስተምራልና፡፡ ‹‹እኔ ራሴ አምላክ ነኝ›› ብሎ ቢያስብ ግን ፈጽሞ ተቀባይነት አያገኝም- ምክንያቱም ከሀይማኖቱ አስተምህሮ ወጣ ያለ ነውና፡፡ ቴሌቭጅን ሳይመጣ በፊት በነበረው ዘመን የነበሩ የስኪዞፈሪንያ ታካሚዎች ‹‹ሀሳቤ ቴሌቭጅን ውስጥ እየተለላለፈብኝ ነው›› አይሉም- ቴሌቭጅን በዛ ዘመን የለምና፡፡ ከዚህ ይልቅ የቅድመ አያቶቻቸው መንፈስ ጣልቃ እየገባባቸው እንደሆነ ሊገልጹ ይችላሉ። በአሁኑ የኮምፒውተሮች እና ኢንተርኔት ዘመን፣ ታካሚዎች ‹‹በኢንተርኔት እየተቆጣጠሩኝ ነው፣›› ‹‹ደብተሬ ላይ አሰርተውብኝ ነው፣›› ‹‹ በመሰለያ መሳሪያ እየተከታተሉኝ ነው›› ሊሉ ይችላሉ፡፡
ዴሉዥኖች የተላያዩ ናቸው፤ በሚከተለው የተወሰኑ የዴሉዥን አይነቶችቶች ተዘርዝረዋል፡፡
የመሳደድ ዴሉዥን (delusions of persecution)

ይህ በጣም የተለመደው የዴሉዥን አይነት ነው። በመሳደድ ዴሉዥን ውስጥ፤ ጣልቃ ገቡብን የሚባሉት አካላት ሕይወት ያላቸው ወይም ግዑዝ፣ ሰዎች ወይም ማሽኖች፤ ከግለሰቦች ወይም ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኛው የሚያሳድደው አካል ማን እንደሆነ ላይለይ ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲሁ የመሳደድ ፍርሀት ይይዘዋል፡፡ የመሳደድ ዴሉዥን (delusions of persecution) የስኪዞፈሪንያ, የባይፖላር እና የድባቴ ወይም የኦርጋኒክ ሕመሞች ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ አጀማመሩም አጣዳፊ ወይም ቀስ በቀስ እያደገ ሂዶ ሥር የሰደደ ሊሆን ይችላል፡፡ የመሳደድ ዴሉዥን (delusions of persecution) ብዙ መልክ ሊኖረው ይችላል። for example
የመጠቋቆም ዴሉዥን (delusions of reference)፡- የመጠቋቆም ዴሉዥን ውስጥ ሕመምተኛው ሰዎች እየተጠቋቋሙበት፣ ስለ እሱ እያወሩ፣ እየሰደቡት፤ እያሙት፣ ወይም እየሰለሉት እንደሆነ ያምናል። ታማሚው በአካባቢው ያሉትን ሰዎች (እንደ ቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤቶች ወይም የቀድሞ ጓደኞች) ወይም የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ቡድኖች እየሰለሉት፣ እየተጠቋቆሙት፣ እያላገጡበት፣ ወይም ስለሱ እያወሩ ሊመስለው ይችላል። አንዳንድ ሕመምተኞች እነሱ ወይም ዘመዶቻቸው ሊገደሉ ነው ወይም እየተሰቃዩ እንደሆነ ያምናሉ። ታማሚው የተለመዱ ክስተቶች ለሱ የተለየ ትርጉም እያስተላለፉ እንደሆነ ያምናል፡፡ ዜና እየተከታተለ ከሆነ ጋዜጠኛ ለእርሱ በምስጢር መልክት እያስተላለፈ እንደሆነ ያምናል፡፡ አንዳንድ የመሳደድ ዴሉዥን ታማሚዎች እየተዘረፍን ነው ወይም ፍትሃዊ ርስት እየተነጠቅን ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ አቃቤ ህግ ሊወስድባቸው የሚፈልገው ልዩ እውቀት እንዳላቸው ይናገራሉ።
የመመረዝ ዴሉዥን (delusions of reference)፡- በከባድ ቅናት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ታካሚዎች የትዳር ጓደኛቸው እየመረዘቻቸው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሌሎች ታካሚዎችም ቤተሰባቸው በምግባቸው ሊመሩዛቸው የሆነ ነገር እንደሚጨመሩባቸው ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ምግብ ሲሰጣቸው በማሽተት ሊያረጋግጡ ይሞክራሉ፡፡
ራስን የመኮፈስ ዴሉሽን (GRANDIOSE DELUSIONS)

ይህ ክስተት እንድ ‹‹ተራ›› ሰው ራሱን እንደ ታዋቂ፣ የተለየ ሀይል ያለው፣ የተለየ ችሎታ ያለው፣ ልዩ የአምላክ መልክተኛ፣ የአምላክ ልጅ፣ ሀብታም ወይም ታዋቂ አድርጎ ሲቆጥር ነው፡፡ ይህ ምልክት ያለባቸው ታካሚዎች እነርሱ ለተለየ ተልዕኮ የተመረጡ መሆናቸውን እና ተልዕኮቻውን እስኪታዘዙ በመጠባቅ ላይ እንዳሉ ሊነግረዋችሁ ይችላሉ፡፡ ፈጣሪ ነኝ፣ የፈጣሪ እናት ነኝ፣ የነገስታት ዘር ነኝ ሊሉ ይችላሉ፡፡ በስራ ላይ አንድ ታካሚ ‹‹የኢትዮጵያን አየር መንገድ የምዘውረው እኔ ነኝ፤ በዓለም ላይ እንደኔ አይነት ሀብታም፣ ታዋቂና ቆንጆ ሰው የለም›› ይለኝ ነበር፡፡
የፍቅር ዴሉዥን (DELUSIONS OF LOVE/ Erotomania)
ይህ ሁኔታ ‘የፋንታሲ አፍቃሪ ሲንድረም’ እና ‘ኤርቶማኒያ’ ተብሎም ይጠራል፡፡ ይህ በጣም ታዋቂ ወይመ ዝነኛ በሆነ ሰው ‹‹ተፈቅሬያለው›› ብሎ ማመን ነው፡፡ኤሮቶማኒያ ከወንዶች በበለጠ በሴቶች ላይ የተለመደ ነው፡፡ ታካሚዋ፤ በእድሜ፣ በዝና እና በሀብት ታዋቂ የሆነ ሰው ከእኔ ፍቅር ይዞታል ብላ በእርግጠኝነት ታምናለች፡፡ ‹‹አፈቀረኝ›› የተባለው ሰው ታካሚዋን ጭራሽ አይቷተም ላያውቅ ይችላል፡፡ በተራራቀ ሀገርም ሊኖሩ ይችላሉ፤ ጭራሽ ተያይተው ላይተዋወቁም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ወጥታ የማታውቅ ሴት ይህ ምልክት ካለባት ‹‹ማይክል ጃክሰን በፍቅሬ ነው የሞተው›› ልትል ትችላለች፡፡ ‹አፍቅሮኛል›› ለተባለው ሰው ደብዳቤ ልትጽፍ ወይም ሌላ ትኩረት የሚስቡ ነገሮችን ልታደርግ ትችላለች፡፡ ድብዳቤ ምላሽ ከሌለው ደብዳቤዎቿ ሆን ተብሎ እየተጠፉባትና አፍቃሪ ለተባለው ሰው እየደረሱ እንዳልሆነ ታምናለች፡፡ ስራ ላይ አንዲት ታካሚ ‹‹ቴዲ አፍሮ ከኔ ፍቀር ይዞት ሊያገባኝ ይፈልግ ነበር፡፡ ቬሎ ለብሼ እንዲወስደኝ እየጠበቁት ነበር ነገር ግን ቤተሰቦቼ ተመቅኝተው እዚህ ሆስፒታል በማስገባት ከእርሱ እንድለይ አደረጉኝ›› ብላኛለች፡፡
የጥፋተኝነት ዴሉዥን (Delusions of Guilt)
ቀላል የድባቴ ሕመም ላይ፤ ታማሚው በተወሰነ ደረጃ ራሱን የሚወቅስ እና ራሱን የሚተች ሊሆን ይችላል። ጥልቅ በሰደደ የድባቴ ህመም ወስጥ ግን እራስን መንቀፍ እጅግ የተጋነነ የጥፋተኝነት ስሜትን ሊሰማው ይችላል፡፡ ታካሚው መጥፎ ወይም ክፉ ሰው እንደሆነ ሲያምን እና ቤተሰቡን ያበላሸ እንደሆነ፣ ይቅር የማይባል ኃጢአት ሠርቻለው ለዚህ በገሃነም ውስጥ እሰቃያለሁ ብሎ ይናገር ይሆናል። በጣም በከፋ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ታማሚው በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ እጅግ በጣም ክፉ ሰው እንደሆነ፣ ከሁሉ እጅግ አስከፊ ኃጢአተኛ እንደሆነ በዚህም ምክንያት በፍፁም እንደማይሞት ነገር ግን እየተቀጣ እንደሚኖ ሊናገር ይችላል።
ብዙውን ጊዜ ራስን ወደ ማጥፋት አልፎ አልፎም ወደ ሌላ ሰውን ወደማጥቃት ይመራሉ፡፡ የቅርብ ዘመዳቸውን በመግደል ራሳቸውን ሊያጠፉም ይችላሉ፡፡ በከፍተኛ ድባቴ የምትሰቃይ እናት ‹‹እኔ ይቅር የማይባል ሀጢአት ሰርቻለው ይህ ደሞ በዘር ስለሚተላለፍ ልጆቼም ላይ አለ›› ብላ ካመነች ይህንን ልታደርገው ትችላለች፡፡
ኒሂሊስቲክ ዴሉዥን (Nihilistic Delusions)
የኒሂሊስቲክ ዴሉዥኖች የሚከሰቱት ታማሚው የአካሉን፣ የአእምሮውን፣ የሚወደውን እና በዙሪያው ያለውን ዓለም መኖሩን ሲክድ ነው፡፡ አእምሮ እንደለው፣ ምንም የማሰብ ችሎታ እንደሌለው ወይም አካላቸው ወይም የአካል ክፍሎቻቸው እንደሌሉ ይናገር ይሆናል። እንደ ሰው መኖርን ሊክድ ወይም እንደሞተ ሊያምን ይችላል፡፡ ዓለም ቆሟል ወይም ሁሉም ሰው ሞቷል ይልም ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኛው በአንዳንድ ድርጊቶች ጥፋትን እንደሚያመጡ ሲያምን፤ የኒሂሊስቲክ ማታለያዎች ከግዙፍ እሳቤዎች ጋር ይዛመዳሉ (ለምሳሌ, አለምን አጥለቅልቀዋለሁ ብሎ ስለሚያምን ለመሽናት እምቢ ይላል)
የድህነት ዴሉዥን (Delusions of Poverty)
የድህነት ዴሉዥን ያለባቸው ታማሚዎች ድሆች እንደሆኑ እርግጠኛ ናቸው እናም ድህነት በእነሱ እና በቤተሰባቸው ላይ እንደተጋረጠ ያምናሉ። እነዚህ ዴሉዥኖች በድባቴ ሕመም ውስጥ የተለመዱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ የመጡ ይመስላሉ።
ሌሎች የዴሉዥን ይዘቶች (other delusion contents)
የአሳሳች መለያዎች (Delusional misidentification)
Delusional misidentification የተለያዩ ሲንድረሞች (የምልክቶች ስብስብ ማለት ነው) መጠሪያ ነው፡፡ ይህም የአንድን ሰው ወይም የቦታ ምንነቱ በሆነ መንገድ ተቀይሯል ወይም ተለውጧል የሚል እምነቶችን ያካትታል፡፡በዚህ ውስጥ የሚጠቃለሉትም ፍሬጎሊ ሲንድረም፣ ካፕግራስ ሲንድረም፣ እራስ-ድርብ ሲንድረም፣ እና ኢንተርሜታሞርፎሲስ ናቸው፡፡
ፍሬጎሊ ሲንድረም (Fregoli syndrome)
ፍሬጎሊ ሲንድረም ያለበት ሰው (ምንም እንኳን በአካል ባይመሳሰሉም) የማያውቀውን ሰው እንደሚያውቀው ሰው አድርጎ ያምናል፡፡ ለምሳሌ፣ የማያውቃትን ሴት እናቴ ናት እንደማለት፡፡ በሌላ አባባል ግለሰቡ የሚያገኛቸው ሰዎች ሁሉ ራሳቸውን ለመደበቅ የሚሞክሩ አንድ አይነት ሰዎች ናቸው ብሎ ማመን ማለት ነው፡፡
ሕመምተኛው፣ የሚቀርበውን ወይም የሚያውቀውን ሰው (አብዛኛውን ጊዜ የቤተሰብ አባልን) በትክክል እርሱን በሚመስል ሌላ ሰው ተተክቷል ብሎ የሚያምንበት ያልተለመደ ሲንድረም ነው። ሕመምተኛው ጓደኛውን፣ የትዳር ጓደኛውን፣ ወላጁን ወይም ሌላ የቅርብ የቤተሰብ አባል (የቤት እንስሳትን ሳይቀር) እነርሱን በሚመስሉ ሌላ እንግዳ አካላት ተተክተዋል ብሎ ያምናል። ብዙውን ጊዜ እድሜ በገፉ ትላልቅ ሰዎች ዘንድ ከመርሳት በሽታ ጋር በተያያዘ ሊከሰት ይችላል፡፡ ለምሳሌ እናቱን ይች ትክክለኛ እናቴ ሳትሆን ሙሉ በሙሉ እናቴን የምትመስል ሌላ እንግዳ ሴት ናት እንደማለት፡፡
እራስ ድርብ ሲንደረም (Syndrome of subjective doubles)
ሙሉ ለሙሉ እኔን የሚመስል ሌላ ሰው አለ ብሎ ማመን ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ‹‹በዚህ አለም ውስጥ ከእኔ ውጭ ሌላ ጋሻው አለ፤ ይህ ጋሻው ሙሉ ለሙሉ እኔን ይሁን እንጅ የሚመራው ግን የራሱን ህይወት ነው ›› ብዬ ባምን እንደማለት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኛው ከአንድ እጥፍ በላይ እንዳለ ይሰማዋል።
ኢንተርሜታሞርፎሲስ (Intermetamorphosis)
ይህ ሲንድረም ሰዎች ተመሳሳይ ፊት እየያዙ ማንነታቸውን ግን ይለዋወጣሉ ብሎ ማመን ነው፡፡ ለምሳሌ ጋሻው አንድን ይህ ሲንድረም ያለበት ታካሚ እሁድ እና ሰኞ ቀን ሄዶ አዋራው እንበል፡፡ ይህ ታካሚ ያዋሩት ሰዎች ‹‹እሁድ ጋሻው ሲሆን ሰኞ ግን የጋሻውን ፊት የለበሰ ከበደ የሚባል ሰው ነው ያዋራኝ›› ብሎ ሊያምን ይችላል፡፡ እሁድ ያገኘሁት ጋሻውን ነው ሰኞ ያገኘሁት ግን ከበደን ነው እንደማለት ነው፡፡
የቁጥጥር ዴሉዥን Delusional control
የቁጥጥር ዴሉዥንም የወል መጠሪያ ሲሆን ሀሳቤን፣ ስሜቴን እና ድርጊቴን የምቆጣጠረው እኔ ሳልሆን ጣልቃ የሚገባብኝ ሌላ አካል አለ ብሎ ማመን ነው፡፡
ታካሚዎች ሀሳባቸውን እንደ ባዕድ እና ከቁጥጥራቸው ውጭ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል፡፡ የማስበው ሀሳብ የኔ ሳይሆን የሌላ አካል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ውሰጥ ሀሰብ ማስገባት፣ ሀሰብ ማቋረጥ፣ እና ሀሳብ ማሰራጨት ይጠቃለሉበታል፡፡
የሃሳብ ማስገባት (Thought insertion)
ይህ ዴሉዥን ያለባቸው ሰዎቸ የማስበውን ነገር የእኔ ሳይሆን ሌላ አካል እያመጣ አእመሮዬ ውስጥ እያስገባብኝ ነው ብለው ያምናሉ።ታማሚው ሀሳቡን ያስገባበት አካል ማን ወይም ከየት እንደሆነ ላያውቀው ይችላል፡፡ ሕመምተኛው ሀሳቦች ወደ አእምሮው እንደሚገቡ ያውቃል እና እንደ ባዕድ እና ከውጭ እንደመጡ ይገነዘባል፡፡ ይህ ምልክት፣ ምንም እንኳን በተለምዶ ከስኪዞፈሪንያ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ በሌሎች የህመም አይነቶች ጋርም ይያያዛል፡፡
የሃሳብ መቋረጥ (thought withdrawal)
ይህ ዴሉዥን ደግሞ እያሰብኩ እያለ በድንገት አንድ አካል ሀሳቤን አውጥቶ ይወስድብኛል ብሎ ማመን ነው፡፡ ለምሳሌ ምሳ እየበላችሁ ባለበት ሰዓት የሆነ አካል የምሳ ገበታችሁን ድንገት ቢያነሳባችሁ እንደማለት ነው፡፡
የሃሳብ ስርጭት (Thought broadcasting)
የሃሳብ ስርጭት ዴሉዥን ሲኖር ታካሚው የሚያስባቸው ሀሰቦች ሌላ ሰው የሚያውቅበት ይመስለዋል፡፡። ይህ ምልክት የታየበት ሰው ሀሳቡ በተለያዩ ሚዲያዎች ለምሳሌ በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ እየተሰራጨ እንደሆነ ሊያስብ ይችላል ። የሃሳብ ስርጭት በብዛት የሚገኘው ስኪዞፈሪንያ ፣ ስኪዞአፌክቲቭ ዲስኦርደር ወይም ባይፖላር ዲስኦርደር ባለባቸው ሰዎች ነው።